አሜሪካ የምንጊዜም ታላቁን የዓለም ዋንጫ ባዘጋጀች ጊዜ

በ ኃይለእግዚአብሔር አድኃኖም ደገፋ
ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም፤ የ2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ዋዜማ ዕለት፤ በአሜሪካ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር AA578 ከዳላስ ፎርት ዎርዝ፤ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው JFK ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለመብረር ተዘጋጅቻለሁ። በአውሮፕላኑ ጫፍ የመጨረሻ ክፍል በሚገኘው የወንበር ቁጥር 33A ቦታዬን ይዤአለሁ። የጉዞ መድረሻ ጊዜው ከምሽቱ ሰዓት ሲሆን፤ አውሮፕላኑ በተያዘለት ሰዓት ጉዞ ሲጀምር፤ ሁሉም ነገር ባቀድኩት መሰረት እየሄደ ይመስል ነበር።
በጉዞዬ ላይ እያለሁ፤ የፊፋ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን በአካል መታደም እና ዘገባ መስራት ምን አይነት ስሜት ሊኖረው እንደሚችል በምናቤ አሰብኩት።
ስፔን ከ አርጀንቲና፤ የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ እንዲሁም የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን ፍልሚያ፣ ላሚን ያማል ከ ሊዮኔል ሜሲ፣ ሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ ከ ሊዮኔል ስካሎኒ፤ ኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ ስታዲየም። የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ያለፉ ጨዋታዎች የእርስ በእርስ ግንኙነቶች፣ የጨዋታው ከፍተኛ ተጠባቂነት፣ የቅድመ ጨዋታው ስሜት እና ግለት ከፍ ማለት፤ እጅግ ተወዳጁ ስፖርት በዓለምአቀፍ ደረጃ እንዲህ ያለ ትልቅ የእግር ኳስ ፍፃሜ ውድድር አስተናግዶ የማያውቅ አስመስሎታል።
የዓለም ዋንጫ የመዝጊያ ስነ ስርአቱ እና የዋንጫ አሰጣጡ ምን ይመስል ይሆን? የዓለም ሻምፒዮን የሚሆነው አገር ማን ይሆን? የውድድሩ ምርጥ ተጨዋች እና የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪስ? ሁሉም አይነት ሃሳቦች በአዕምሮዬ ይመላለሳሉ።
ኒው ዮርክ እንደደረስኩ፤ ወደ ማረፊያ ክፍል ከመሄዴ በፊት አደርጋቸዋለሁ ብዬ ያቀድኩዋቸው ጉዳዮችም አሉ። በቅድሚያ ጓደኛዬን ማግኘት፣ ቀጥሎ የከተማዋ ልዩ መገለጫ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት. . . በእንዲህ አይነት ሀሳብ መሃል ስልኬን ከአውሮፕላን በረራው ዋይፋይ ጋር አገናኝቼ፤ በማያሚ ስታዲየም እንግሊዝ ከ ፈረንሳይ የሚያደርጉትን የደረጃ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ መከታተል ጀመርኩ፤ የቀጥታ ስርጭቱ ጥራት አስደናቂ በመሆኑ ምርጡን ጨዋታ ያለምንም መቆራረጥ ተመልክቼ ዘና አልኩ።
በ2026 ዓለም ዋንጫ ውድድር ከታዩ ምርጥ እና አዝናኝ ፉክክሮች አንዱ የሆነውን የደረጃ ጨዋታ እንግሊዝ 6ለ4 ስታሸንፍ፤ ቡካዮ ሳካ ሃትሪክ ሰራ። ዴክላን ራይስ እና ኤዝሪ ኮንሳ እንዲሁም ጁድ ቤሊንግሃም ከመሃል ሜዳ ኳስ እየነዳ በመሄድ ከውድድሩ ምርጥ ጎል እጩዎች አንዱን አስቆጠረ።
ፈረንሳይ በመጀመሪያው አጋማሽ 4ለ0 መመራቷ አስደንጋጭ ነበር። በፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታቸውን የመሩት አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሾ ከእረፍት መልስ ለውጦችን በማድረግ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክረዋል። ቢሆንም ግን የኪሊያን ምባፔ ሁለት እና የብራድሌይ ባርኮላ እንዲሁም ኦስማን ዴምቤሌ ጎሎች ውጤቱን ለመቀልበስ በቂ አልነበሩም። ነገር ግን አምበሉ ኪሊያን ምባፔ በ10 ጎሎች በተከታታይ ሁለት ዓለም ዋንጫዎች የወርቅ ጫማ አሸናፊ ሲሆን፤ በዓለም ዋንጫው ታሪክ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን ከሊዮኔል ሜሲ በአንድ ጎል በልጦ፤ በ22 ጎሎች ቀዳሚ በመሆን አጠናቅቋል።
በ2026 ዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ከሀገሩ ውጪ በተዘጋጀ ውድድር ምርጡን ውጤቱን ሲያስመዘግብ፤ ዉጤቱ ለሶስቱ አናብስት በ1966 የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን ከሆኑ ወዲህ በ60 ዓመት ውስጥ ያስመዘገቡት ከፍተኛው ደረጃ ሆኗል።
የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሾ የ14 ዓመታት ቆይታው የመጨረሻ ጨዋታው ውጤት አራተኛ ደረጃ አስገኝቶለት ተጠናቅቋል። ከስምንት ዓመታት በፊት ሩሲያ ላይ የዓለም ዋንጫን ያሸነፈው ዴሾ፤ በተጨዋችነት እና በአሰልጣኝነት የዓለም ዋንጫን በማሸነፍ ከብራዚላዊው ማሪዮ ዛጋሎ እና ጀርመናዊው ፍራንዝ ቤከንባወር ጋር ታሪክ መስራቱ ይታወሳል።
ጨዋታውን ተመልክቼ ካጠናቀቅሁ በኋላ፤ ራሴን ዘና ለማድረግ እና የምድሪቱን ግዙፍ የስፖርት ሁነት ያለፉት 38 ቀናት ቆይታን ወደ ሗላ ተመልሼ ለማስታወስ ሞከርኩ።

ክብረወሰኖችን ከሰባበሩት የዓለም ዋንጫው አዘጋጆች እስከ ተሳታፊ ሀገራት አስደናቂ የደጋፊዎች ባህል እና መስተጋብር. . .
በተለምዶ ትንሽ የሚባሉ እና አዳዲስ የእግር ኳስ ሀገራት አስገራሚ የጨዋታ ብቃት. . .
ትልልቅ ስም ያላቸው ኮከቦች እንደተጠበቁት ምርጥ ብቃታቸውን ያሳዩበት. . .
ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች. .
ጥራት ያለው የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እና
በሁሉም ዘርፎች ክብረወሰኖች የተሰባበሩበት ዓለም ዋንጫ ነበር።
ሚያዚያ 20/2018 ዓ.ም የፊፋ ዓለም ዋንጫ ውድድርን እንደ ጋዜጠኛ ሽፋን ለመስጠት ፍቃድ ሲሰጠኝ፤ ወሩን ሙሉ እንዲህ ባለ የሚያስደንቅ ስሜት እሞላለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር። በተለይም ከ10 ዓመታት በላይ በቆየሁበት ሙያ ከዓለም ዋንጫ በስተቀር፤ የኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን የመከታተል ልምዱ ለነበረኝ ለእኔ፤ ይሄኛው አጋጣሚ ከገመትኩት በላይ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል።
በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በአካል ተገኝቼ የመመልከት እድሉን ያገኘሁት፤ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ኩራሳኦ ከአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኗ ጀርመን ያደረጉትን ጨዋታ ነው።
68ሺ ተመልካቾችን የሚያስተናግደው የሂዩስተን ስታዲየም በአብዛኛዉ ነጭ በለበሱ ደጋፊዎች ከአፍ እስከ ገደፋ ሞልቷል። ጨዋታውን ጀርመን 7ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈች። የስታዲየሙ ድባብ እጅግ አስደናቂ፤ ሁሉ ነገሩ ፍፁም የተለየ ነው። እንደጠበቅኩት ጨዋታው የአንድ ቡድን የበላይነት የታየበት ቢሆንም፤ ፋክክሩ አዝናኝ ሆኖ አልፏል። በመጀመሪያው 45 ደቂቃ በብዙ ነገር እጅግ በመደነቄ: ኹነቱ ላይ መገኘቴ ህልም ሳይሆን እውን መሆኑን ደጋግሜ ለራሴ መንገር አስፈልጎኛል፤ ቀጥሎ አካባቢዬን ስቃኝ ግን፤ ከእኔ በስተቀር ሁሉም ባለሙያ ስለ ጨዋታው ማስታወሻ በመያዝ ስራ ላይ ተጠምዷል። ጥሩው ነገር ጨዋታውን በሚገርም ማስተዋል እያየሁ በመሆኑ ሁሉንም በአእምሮዬ እየመዘገብኩ ነበር። የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሽ ዋና ዋና ሁነቶች ማስታወሻዬ ላይ ለመፃፍ ስነሳም አንድም ነገር ሳልስት ማስፈር ችያለሁ።
ውድድሩ እየቆዬ በሄደ ጊዜ እንኳን ይህ የመደነቅ ስሜቴ ሊቀንስ አልቻለም። ከ20 በላይ ብሄራዊ ቡድኖችን ጨዋታዎች: አብዛኞቹን ደጋግሜ: በአካል የመከታተል እድሉን አግኝቻለሁ። የአርጀንቲና፣እንግሊዝ፣ ፖርቱጋ እና ስፔንን ጨምሮ የኖርዌይ፣ ብራዚል፣ ግብፅ፣ ኮትዲቯር፣ ሞሮኮ: ክሮሺያን እና ሌሎችንም ጨዋታዎች ተመልክቻለሁ። የእግር ኳሱን ትልልቅ ኮከቦች ቅድመ እና ድህረ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ክፍት የልምምድ ክፍለ ጊዜዎችን እና ጨዋታዎቻቸውን በቅርበት የመመልከት ትልቅ እድልን አጣጥሜያለሁ።
የእግር ኳሱ ዓለም ኮከቦች ከጠበቅኩት በላይ ስራቸውን የበለጠ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ እንደሚያከናውኑ አስተውያለሁ።
በስፖርቱ ዝነኛ ከሆኑ ተጨዋቾች እና በጋዜጠኝነት ከሚከበሩ ትልልቅ ሙያተኞች ጋር ሃሳብ የመለዋወጥ እና እውቀት የመገብየት እድሉን አግኝቻለሁ። በዓለም ዋንጫው ሁነት መደነቄን ሳላቆም፤ በእያንዳንዱ ቀን ትምህርት የወሰድኩበት እና ልምድ የቀሰምኩበት ውድድር ሆኖ አልፏል።

አሜሪካ የራሷን ማንነት ለዓለም ያሳየችበት. . .
የ2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫ ግዙፍነት አያጠያይቅም። በአይነቱ ለየት ያለ እና በሁለም መስክ ክብረወሰኖች የተሰባበሩበት ከምንም በላይ የአሜሪካን 250ኛ ዓመት ክብረበአል ለማሰብ ምርጥ አጋጣሚም ሆኖ አልፏል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ በሶስት ሃገራት የጋራ አዘጋጅነት ተሰናድቷል። ከ104ቱ ጨዋታዎች 78ቱ፣ ከ16 የውድድር አዘጋጅ ከተሞች 11ዱ በአሜሪካ፤ ሲገኙ ካናዳ እና ሜክሲኮ እያንዳንዳቸው 13 ጨዋታዎችን አስተናግደዋል። የሜክሲኮው አዝቴካ ጨዋታ ካስተናገዱ 3 ስታዲየሞች አንዱ ሲሆን፤ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ሶስት የመክፈቻ ጨዋታዎችን በማስተናገድ የመጀመሪያው ነው። አዝቴካ ስታዲየም ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን 2ለ0 ያሸነፈችበትን የ2026 ዓለም ዋንጫን ጨምሮ፤ በ1970 እና 1986 የመክፈቻ ጨዋታዎችን አስተናግዷል።
በውድድሩ ጊዜ ሁሉ አሜሪካ ምን ያህል ሰፊ እና ታላቅ ሃገር እንደሆነች፤ ህዝቦቿ እንግዳ ተቀባይ እና የሁሉም ህዝብ መኖሪያ መሆኗን ለዓለም አሳይታለች። በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ የሆኑ አብዛኞቹ ሀገራት በተጓዥ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን፤ ሰፊ በሆነው የዲያስፖራ ማህበረሰብ እና ስፖርት ወዳድ ከሆኑ አሜሪካውያን ጭምር በየስታዲየሙ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙበት ሆኗል። በዚህም እያንዳንዱ ብሄራዊ ቡድን በገዛ ሀገሩ የሚጫወት እስኪመስል ድረስ ከተመልካቾች ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝ ነበር።
ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ስታዲየሞች፣ አስደናቂ ድባብ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች የ2026 ዓለም ዋንጫ ልዩ መገለጫዎች ናቸው።
6.8 ሚሊዮን ህዝብ በስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታዎችን ተከታትሏል፣
በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ተመልካቾች ከይፋዊ የደጋፊዎች ፌስቲቫል ቦታ ሆነው በትልልቅ ስክሪኖች ተመልክተዋል፣
48 ሀገራት ተሳትፈዋል፣
308 ጎሎች ተቆጥረዋል፣
15 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፣
6 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ በቴሌቭዥን መስኮት የዓለም ዋንጫውን ተከታትሏል።
ፊፋ ከውድድሩ ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል። በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ የዓለም ዋንጫው ክብረወሰኖች የተሰባበሩበት ሆኖ ተጠናቅቋል።
ተጓዥ ደጋፊዎች ውድድሩን በተመለከተ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ያጋሩት ግብረመልስ እና ሰውኛ ታሪኮች የዓለም ዋንጫው እጅግ ስኬታማ ለመሆኑ ተጨማሪ ምስክር ናቸው። ዓለም ዋንጫው ከውድድር ባለፈ ትልቅ አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍም አሳይቷል። ውድድሩን በተመለከተ በቀጥታ አስተያየት እንዲሰጡኝ የጋበዝኳቸው ሰዎች በሰጡኝ ምላሽ፤ እግር ኳስ የሰዎችን የቆዳ ቀለም፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነቶችን ተሻግሮ ሁሉንም አንድ የማድረግ አቅም እንዳለው የተመለከቱበት ውድድር እንደሆነም ነግረውኛል።
እጅግ አስደናቂ ውድድር እና ውብ ፉክክር ስመለከት ቆይቼ አንድ ጨዋታ ብቻ ቀርቶኛል። የጨዋታ ቁጥር 104፤ ግዙፋ የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ፍልሚያ ብቻ!

በዚህ አስደናቂ የዓለም ዋንጫ የትዝታ ባህር በሰጠምኩበት ጊዜ፤ ከአውሮፕላኑ የበረራ ክፍል የመጣው ድምፅ በድንገት አነቃኝ። ፓይለቱ አንድ መልእክት ደጋግሞ አሰማ፤ “በኒው ዮርክ ባለው ከባድ ዝናብ እና ነጎድጓዳማ የአየር ፀባይ ምክንያት፤ በዚህ ቅፅበት በJFK ኤርፖርት ማረፍ አንችልም። በመሆኑም ድንገተኛ ማረፊያ ለመጠቀም ባልቲሞር ወደሚገኘው BWI ኤርፖርት እንጓዛለን። በዚያም የአየር በረራ ተቆጣጣሪዎች ወደ ኒው ዮርክ መመለስ እንደምንችል እስኪያሳውቁን እንጠብቃለን” ሲል ተናገረ። በባልቲሞር ሰማይ ላይ አንድ ሰዓት ለሚጠጋ ጊዜ ካንዣበብን በኋላ፤ በአየር ማረፊያው ምድር ላይ ለተጨማሪ አንድ ሰዓት አውሮፕላኑ በዝግታ ይንቀሳቀስ ነበር። በመጨረሻም ምሽት 5:00 ሰዓት ላይ ፓይለቱ በድጋሚ ተመልሶ፤ ምሽቱን በባልቲሞር እንደምናሳልፍ እና በረራችን ወደ ቀጣዩ ቀን 05:15 መቀየሩን አሳወቀን።
ለዚህ ድንገተኛ ዱብ እዳ ስላልተዘጋጀሁ፤ በጣም ደነገጥኩ። የነበረኝ ደስታ እና ጉጉት ሁሉ ወዲያው ወደ ከባድ ጭንቀት ተቀየረ። ምክንያቱም በመንገድ መዘጋጋት እና በደህንነት ጉዳይ መዘግየት እንዳይፈጠር፤ ፊፋ ፍቃድ ለተሰጣቸው የሚዲያ አካላት ከቀኑ 06:30 በፊት ስታዲየም እንድትደርሱ ሲል አስቀድሞ መልእክት ልኮ ነበር።
ቀደም ብለው ወደ ኒው ዮርክ የሚጓዙ ሌሎች አየር መንገዶች ካሉ ተመለከትኩ። መስኮት ላይ የሚገኙ የበረራ ባልደረቦችን አናገርኩ፤ ሌላ የበረራ ቲኬት ግን አልተገኘም። ወዲያውኑ ሁለተኛ አማራጬን ለመጠቀም ወሰንኩ። በባቡር መጓዝ! መደበኛ የባቡር ቲኬት ለማግኘት ያደረኩት ጥረት አልተሳካም። ነገርግን አምስት ሰረገላ ያለው የባቡሩ ወንበር በሙሉ በመደበኛ ትኬት ተጓዦች በመያዙ፤ እድለኛ ሆኜ የቀረችዋን አንድ የቢዝነስ ክላስ ቲኬት በውድ ዋጋ አገኘሁ።
ሌሊቱን በአየር ማረፊያው አሳለፍኩ። ከጥቂት ሰአታት በኋላ ከአየር መንገዱ ሌላ የኢሜል መልእክት ደረሰኝ፤ ለ05:15 ተቀጥሮ የነበረው በረራ በድጋሚ ወደ ቀን ዘጠኝ ሰዓት እንዲዘገይ መደረጉን ይገልፃል። የተቀየረው አዲስ የበረራ ሰዓት ማለት በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር የፍፃሜው ጨዋታ የሚጀመርበት ጊዜ ነው። ጭንቀቴ ከፍ እያለ መጣ። ባቡሩ እንዲዘገይ ቢደረግስ? የቴክኒክ ብልሽት ቢገጥመውስ? ቦታ የለም ሞልቷል ብባልስ? የዓለም ዋንጫ የፍፃሜው ጨዋታ ሊያመልጠኝ ማለት ነው? ከባድ ጭንቀት...
በሚገርም ግጥምጥሞሽ፤ ከሶስት ቀናት በፊት ከዓለም ዋንጫው አዝናኝ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው፤ አርጀንቲና እንግሊዝን 2ለ1 ያሸነፈችበትን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ለመመልከት ከዳላስ ወደ አትላንታ ተጉዤ፤ በዚያው እለት ተመልሸ ነበር።
ምንም እንኳን ለዚህ ጉዞ ከቤቴ ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት ላይ ብወጣም፤ ከዳላስ ወደ ናሽቪል የነበረኝ የመጀመሪያ በረራ እና ወደ አትላንታ የነበረኝ ተያያዥ በረራዎች በመዘግየታቸው ምክንያት፤ ጨዋታው ከመጀመሩ 15 ደቂቃዎች በፊት ስታዲየም ለመድረስ ቻልኩ። እንደአለመታደል ሆኖ ግን፤ የስቴዲየም ደህንነት ተቆጣጣሪዎች የጀርባ ቦርሳ መለያ ታግ በመጨረሳቸው ምክንያት፤ እኔን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ሰልፍ ላይ ለመጠበቅ ተገደድን። በዚህም የአርጀንቲና እና እንግሊዝ ጨዋታ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች አመለጡን። ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት እንዲሆን የማልመኘው ዋነኛ ነገርም፣ በድጋሚ በእንደዚህ አይነት አስጨናቂ ሂደት ውስጥ ማለፍን ነዉ::

በተጠበቀው ልክ ሁልጊዜ ደስታን የሚሰጠው ውብ ጨዋታ - እግር ኳስ!
በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታዲየም ገብቼ ከተመለከትኩት፤ የጀርመን እና ኩራሳኦ ጨዋታ እሰክ ታላላቆቹ ስፔን ከ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ከ አርጀንቲና የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያዎች ድረስ፤ የታላላቆቹን የእግር ኳስ ሃገራት ትንቅንቅ በአይኔ ተመልክቻለሁ። ከሜሲ እጅን በአፍ የሚያስጭን ምርጥ ብቃት እሰከ ሮናልዶ፣ ኑዌር፣ ሞድሪች እና ኔይማር አሳዛኝ የዓለም ዋንጫ ስንብት። ከኪሊያን ምባፔ ምትሃታዊ ጎሎች እሰከ ማይክል ኦሊሴ፣ ጁድ ቤሊንግሃም እና ሃሪ ኬን አስደናቂ ብቃት፤ በሜዳ ላይ ስኬቱ እና ከሜዳ ውጪ በማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች ተወዳጅ እስከሆነው፤ ሀገሩ ኖርዌይን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ያደረሰው ኧርሊንግ ሃላንድ ድረስ የታላላቆቹን ኮከቦች የእግር ኳስ ተዓምር በሜዳ ላይ አጣጥሜያለሁ።
ከኬፕ ቨርዱ ግብ ጠባቂ ቮዢንሃ ጀግንንት የተሞላበት የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎ እና እፁብ ድንቅ ብቃት እሰከ አስደናቂው የኔዘርላንድስ ብርቲካናማዎቹ አስገራሚ የድጋፍ ባህል፤ ከኖርዌይ ደጋፊዎች ዝነኛው “ሩ” እስከ አርጀንቲና እና ሜክሲኮ ለቡድናቸው እጅግ ጥልቅ ፍቅር ባላቸው ደጋፊዎች ተደምሜያለሁ። ከእንግሊዝ እና አሜሪካ ጨዋታዎች በኋላ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች በስታዲየም ውስጥ በጋራ የሚጫወቷቸው እና ኮንሰርትን የሚያስንቁት “ስዊት ካሮላይን”፣ “ዎንደርዎል” እና “ቴክ ሚ ሆም” ሙዚቃዎችን በህብረት ሲያዜሙም ተገርሚያለሁ።
በዚህኛው የዓለም ዋንጫው ማንፀባረቅ የቻሉት፤ ከዚህ ቀደም ዝነኛ የሆኑ ኮከብ ተጨዋቾች ብቻም አይደሉም። የወደፊት ተስፈኛ ኮከቦቹ ሜክሲኳዊው ጂልቤርቶ ሞራ፣ የስፔኖቹ ፓው ኩባሬሲ እና ላሚን ያማል የወደፊት የስፖርቱ ንግስና አልጋ ወራሾች እንደሚሆኑ አሳይተዋል። የዓለም ዋንጫን ያዘጋጁት ሶስቱ ሀገራትም ወደ 16 ውስጥ ጥሎ ማለፍ ዙር በመግባት ስኬታማ ጉዞ አድርገዋል።
የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኬፕ ቨርድ እና ዝቅተኛ ግምት የተሰጣቸው እንደ ግብፅ፣ ኮሎምቢያ፣ ኖርዌይ፣ ዲአር ኮንጎ እና ስዊዘርላንድ እንዲሁም ሌሎቹ ሀገራት ያሳዩት አስገራሚ አቋም፤ የዓለም እግር ኳስ የፉክክር ደረጃ እየተቀራረበ መሆኑን በማሳየታቸው፤ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥርን ከ32 ወደ 48 ማሳደጉ ተገቢ እንደሆነ አረጋግጠዋል። የብራዚል፣ ፖርቱጋል፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድስ በጊዜ ከውድድሩ መሰናበትም የእግር ኳስን አይገመቴነት አንዱ ማሳያ ነበር:: አስገራሚ የውጤት ቅልበሳዎች፣ በርከት ያሉ የመጨረሻ ደቂቃ ልብ ሰባሪ ጎሎች፣ ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ ያሉ ውዝግቦች፣ ክሶች እና የሴራ ንድፈ ሃሳቦች፣ ውብ እና ደማቅ የመክፈቻ እና መዝጊያ ስነስርአቶች፤ የማራኪው ጨዋታ መገለጫ የሆኑ ሁሉም አይነት ሁነቶች በውድድሩ ላይ ደምቀው መታየት፤ ዓለም ዋንጫውን በመላው ዓለም በቢሊዮን በሚቆጠሩ የእግር ኳስ ወዳጆች ዘንድ ፈፅሞ የማይረሳ፤ ሁሌ የሚታወስ መድረክ እንዲሆን አድርጎታል።
የፍፃሜው ጉዞ
ከጠዋቱ 01:55 ሲሆን፤ ጉዞ ከBWI ቱርጉድ ማርሻል ባቡር ጣቢያ ወደ ኒው ጀርሲ፣ ኒዋርክ ፔን ባቡር ጣቢያ፤ ጉዞዬ በተያዘለት ሰዓት በመጀመሩ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። የዓለም ዋንጫ ምርጥ አጋጣሚዎቼን እና ያሳለፍኩትን ደስ የሚል ጊዜ እያሰብኩ፤ የሶስት ሰአቱን የባቡር ጉዞ አጠናቀቅኩ።
የምንጊዜም ታላላቅ ተጫዋቾች ዝርዝር ወስጥ ቀዳሚ የሆኑት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲን፤ ከያማል፣ ምባፔ፣ ቤሊንግሃም እና ኬን፤ እንዲሁም ዲዲዬ ዴሾ፣ ካርሎ አንቼሎቲ፣ ሮናልድ ኮማን፣ ሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ፣ ሊዮኔል ስካሎኒ እና ቶማስ ቱኬልን በአካል ማግኘት እና በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፤ ከአንደበቶቻቸው ከሚወጡ ቃላት ለስራ ዘገባዬ የሚሆኑ ሃሳቦችን መውሰድ፤ በህልም ዓለም ውስጥ ያለሁ ያክል እንዲሰማኝ አድርጓል። ምክንያቱም ለዓመታት እነዚህን የእግር ኳስ ግዙፍ ልዕለሰቦች በቴሌቭዥን መስኮት ተመልክቻቸዋለሁ። ሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮችን እና ሌሎች የሚዲያ ዜናዎችን በመጠቀም ታሪኮቻቸውን አዘጋጅቻለሁ።
አሁን ግን፤ ለዓመታት እንደ መረጃ ምንጭ እጠቀማቸው ከነበሩ ትልልቅ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች ጎን ለጎን ቁጭ ብዬ፤ ዘገባዎቻቸውን እንዴት እንደሚቀርፁ እና ፕሮፌሽናል ስራቸውን የሚከውኑበትን መንገድ መማር ለእኔ ትልቅ አጋጣሚ ነበር።

የቀድሞው ታላላቅ ተጨዋቾችን፤ እንደ አለን ሺረር፣ ዌይኒ ሩኒ፣ ዳኒ መርፊ፣ ማርሴል ዴሳዬ፣ አንድሬ ሼቭቼንኮ እና ሌሎች፤ እንዲሁም ዝነኛ የእግር ኳሱ ዓለም ፀሃፍት ጆናታን ዊልሰን: ጊዬም ባላጌን እና ፍቅር ይልቃልን አግኝቼ ከልምዳቸው ትምህርት መውሰድ እና ምክራቸውን መቀበል ለእኔ በዋጋ ሊተመን የማይችል ትልቅ አጋጣሚ ነው። ከፍተኛ ፉክክር ባለበት ከባቢ ውስጥ መረጃ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብኝ፤ ተጫዋቾች ለጥያቄዎች መልስ ለመመለስ በማይገደዱበት ሚክስድ ዞን እና ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እንዴት የጥያቄ እድሎቼን መጠቀም እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። ጋዜጠኞች መረጃ በፍጥነት ለመስጠት እና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ትግል አይቻለሁ። ከምንም በላይ ግን ለሙያ መታመንን እና ስራን በአግባቡ ማከናወን የሚያስገኘውን ክብር ተመልክቻለሁ። ሙያን አክብሮ መስራት መልካም ስም እና ትልቅ ክብር ሲሰጠው አስተውያለሁ። አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ 18 ዓለም ዋንጫዎችን ለዘገቡት አንጋፉ አርጀንቲናዊ ጋዜጠኛ ኤንሪኬ ማርኬዝ የሰጡት አክብሮት ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም። የ91 አመቱ ጋዜጠኛ፤ አርጀንቲና ከ ጆርዳን ከመጫወቷ አስቀድሞ አምበሉ ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታው በቋሚነት ስለመጀመሩ ለስካሎኒ ላቀረቡት ጥያቄ፤ አሰልጣኙ ለአንጋፋው ጋዜጠኛ ክብር ሲል፤ የሜሲን የመሰለፍ ጉዳይ ከአንድ ቀን በፊት በልዩ ሁኔታ መልስ ሰጥተውበታል። እንደ ጋዜጠኛ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ውድድርን ዘገባ እንዴት መስራት እና ሽፋን መስጠት እንዳለብኝ ተምሬበታለሁ።
የፍፃሜው ጨዋታ
የ2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ከጨዋታም በላይ ነበር። የአሜሪካ የመዝናኛው ዓለም ዝነኞች የፊልም ኮከቦች፣ ሙዚቀኞች እና ታላላቅ የቀድሞ ስፖርተኞች ታድመዋል። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሜክሲኮዋ ክላውዲያ ሼንባውም እና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስቴር ማርክ ካርኔይ እና የስፔኑ ንጉስ ፊሊፔ ስድስተኛ ከሌሎች የክብር እንግዶች ጋር በኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ ተገኝተዋል።
ስታዲየም የደረስኩት ከጨዋታው መጀመር ሶስት ሰዓታት ቀደም ብሎ ነው። ይሰማኝ የነበረው ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ጥርጣሬ እና ድካም ሙሉ በሙሉ ለቅቆኛል። እረፍት የማግኘት እና የደስታ ስሜት ሲወረኝ ይታወቀኛል። በስታዲየሙ ሰሜናዊ ክፍል ወደ ተዘጋጀልኝ መቀመጫ ብሎክ 201: ቁጥር 194 B ስራመድ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን ሁሉ ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው።

በትልቅ ጉጉት የተጠበቀው ጨዋታ ተጀመረ። የዓለም አይኖች ሁሉ ስፔን ከ አርጀንቲና በሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ ተተክለዋል። የሊዮኔል ሜሲ ሌላ ተአምር ይኖር ይሆን? ወይስ በግማሽ ፍፃሜ ለዋንጫ ተጠባቂዋ ፈረንሳይ ላይ ፍፁም ብልጫ የወሰደው በሮድሪ የሚመራው የስፔን ብሄራዊ ቡድን? ባለ ተሰጥኦው ላሚን ያማል በመጨረሻ ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ቀጣይ የእግርኳሱን ንግስና ከሜሲ ይረከብ ይሆን? በርካታ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱ።
ስፔኖች በጨዋታው በጣም ጠንካራ የነበሩ ሲሆን፤ በተለመደ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ጥሩ አጀማመር አድርገዋል።
የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን አርጀንቲና ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ ቅርፃቸውን ጠብቀው በጥልቀት በመከላከል፣ ጎል አለማስተናገድን የጨዋታ እቅዳቸው አድርገው ተከላክለው ወጥተዋል። በአርጀንቲና በኩል ምንም አይነት የማጥቃት ፍላጎት አልታየም። በዓለም ዋንጫው ሌሎች ጨዋታዎች እንደታየው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ለማጥቃት ጉልበታቸውን እየቆጠቡ ይመስል ነበር። ነገር ግን የአርጀንቲና ማጥቃት ሳይታይ በሙሉ 120 ደቂቃዎች አንድም ኢላማውን የጠበቀ የጎል ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በስፔን ፍፁም የበላይነት ተጠናቀቀ።
አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞላ በተቃረበው ዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ልክ እንደ አሜሪካኖቹ ሱፐር ቦል፤ የእረፍት ሰዓት የሙዚቃ ድግስ ተዘጋጅቷል። ዝነኞቹ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች ማዶና፣ ጀስቲን ቢበር፣ ሻኪራ እና ቢቲኤስ በስታዲየም ለተገኙ 82ሺ ደጋፊዎች እና በቢሊዮን ለሚቆጠሩ በመላው ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት ዝግጅቱን ለሚከታተሉ ሰዎች የሙዚቃ ዝግጅታቸውን አቅርበዋል። ምንም እንኳን በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የእረፍት ሰዓት የሙዚቃ ድግስ በአዲስ መልክ መጨመሩ ሁሉንም የሚያስማማ ሀሳብ ባይሆንም፤ የሙዚቃ ድግሱ ለውቡ ጨዋታ አዲስ ልምድ እና የተለየ ተጨማሪ ቀለም የሰጠ በመሆኑ በግሌ በጣም ተደስቻለሁ።

ሁለተኛው አጋማሽም ከመጀመሪያው ብዙ ልዩነት አልታየበትም። በመጨረሻም ፌራን ቶሬስ በ106ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል፤ በቅርብ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ታሪክ ባልታየ መልኩ ስፔን በወቅቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን አርጀንቲና ላይ ፍፁም የበላይነት በመውሰድ ከ16 ዓመታት በኋላ ሁለተኛ የዓለም ዋንጫዋን አሸንፋለች።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያለሙ ቅያሪዎች ተደርገዋል። ነገር ግን የስፔን የበላይነት በርትቶ፤ በሜሲ የሚመራው አርጀንቲና የጨዋታ ተፅእኖ ሳይታይ ቀርቷል። ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የቀጠለ፤ ስፔኖች የበለጠ ቀጥተኛ አጨዋወት የመረጡበት እና ወደ ግብነት ያልተቀየሩ በርካታ እድሎች የፈጠሩበት ሆኗል። ስፔን በአንድ በኩል የአጨራረስ ድክመት፤ በሌላ በኩል ደግሞ አስደናቂው ግብ ጠባቂ ኤሚ ማርቲኔዝ በፍፃሜ ክብረወሰን የሆነ 11 ሙከራዎችን በማዳን ምርጥ የነበረበት ጨዋታ በመሆኑ ተጨማሪ ጎሎችን ሳታገኝ ቀርታለች።
በፍፃሜው አርጀንቲናን ከድጡ ወደ ማጡ የከተተ ክስተትም ተፈጥሯል። በግማሽ ፍፃሜው ጀግና የነበረው ኤንዞ ፈርናንዴዝ፤ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሲል ፓው ኩባርሲ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በዚህም አርጀንቲና ተጨማሪ 30 ደቂቃዎችን በጎደሎ ተጨዋቾች ለመጨረስ ተገዳለች። በ10 ተጨዋቾች መጫወት የአርጀንቲናን ሞራል እና ስሜት የገደለ፤ ጨዋታውን የማሸነፍ ትንሽ ተስፋንም ገደል የከተተ ነበር። ምክንያቱም በተጨማሪ 30 ደቂቃ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ጎል ማስተናገዳቸው፤ ጨዋታውን ወደ መለያ ምቶች የመውሰድ እና ከአራት ዓመት በፊት ካታር ላይ የሰሩትን ታሪክ የመድገም ተስፋቸውን ሙሉ ለሙሉ አጨልሞታል።
ሊዮኔል ሜሲ ለረጅም ጊዜ የአርጀንቲናን ቡድን ተሸክሞ ለድሎች አብቅቶታል ወይም ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ የእርሱ ጥገኛ ሆኗል። ነገርግን በሚገባ የተደራጀው እና የተዋሃደው፤ በቴክኒክ የላቁ ተጨዋቾችን የያዘው እና የተለየ ግልፅ የጨዋታ መንገድ ያለውን ይህንን የስፔን ቡድን ማሸነፍ፤ በሜሲ ደረጃ ያለ ባለተሰጥኦ ኮከብ ለያዘው አርጀንቲና እንኳን የሚቻል አልሆነም።
የ2026 ፊፋ ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ስፔንን የ21ኛው ክፍለዘመን እጅግ ስኬታማው ብሄራዊ ቡድን በማድረግ ተጠናቋል። ስፔን ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም ወዲህ ሁለት የዓለም ዋንጫዎች እና ሶስት የአውሮፓ ዋንጫ ክብሮችን አሸንፋለች። ከፍፃሜው በኋላ የአርጀንቲና ተጨዋቾች ያሳዩት ስነምግባር የጎደለው ያልተገባ ባህሪ፣ ፀብ እና ረብሻ ደግሞ የተጨዋቾቹን መጥፎ ጎን ለዓለም ያሳየ ነበር።
የአርጀንቲና ተጨዋቾች እና አንዳንድ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የፈጠሩት አምባጓሮ፤ ስፔን ዋንጫውን ስታነሳ ጀርባቸውን በመስጠት ሻምፒዮኖቹን ክብር የነፈጉበት መንገድ በእግር ኳሱ ዓለም እጅግ አሳፋሪ ተግባር ሆኖ ታይቷል።

የግል ሽልማቶች
ለስፔን በዓለም ዋንጫው በተለይ ከጥሎ ማለፍ በኋላ የነበራት ፍፁም የበላይነት፤ በጣም አስፈላጊውን የቡድን ዋንጫ ያነሱበት እና በመለያ ደረታቸው ላይ ሁለተኛውን ኮከብ ያሰፈሩበት ብቻ ሳይሆን፤ በውድድሩ ምርጥ ብቃት የነበራቸው አራት ተጨዋቾቻቸውም በተለያዩ ዘርፎች የተሸለሙበት ሆኗል።
• የወርቅ ኳስ - ሮድሪ - ስፔን
• የፍፃሜው ጨዋታ ምርጥ ተጨዋች - ፌራን ቶሬስ - ስፔን
• ወርቃማ ጓንት - ኡናይ ሲሞን (በ7 ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት፤ አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮበታል) - ስፔን
• የውድድሩ ምርጥ ወጣት ተጨዋች - ፓው ኩባርሲ - ስፔን
• ወርቃማ ጫማ - ኪሊያን ምባፔ - ፈረንሳይ (10 ጎሎች) በ22 ጎሎች የዓለም ዋንጫው የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ
• ብዙ ጎል የሆኑ ኳሶችን ያቀበለ - ማይክል ኦሊሴ - ፈረንሳይ (7 አሲስት)

የዓለም ዋንጫ ቆይታዬ እጅግ በጣም አስደናቂ እና በእኔ ሙያ የህይወት ዘመኔ ከትላልቆቹ አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። ምንአልባትም በህይወት ዘመን አንዴ የሚገኝ እና ሁልጊዜ በበጎ የማስታውሰው ትልቅ ታሪኬ ሆኖ ተጠናቋል። ፊፋ እና አሜሪካ በዓለም ዋንጫ ታሪክ እጅግ አይረሴውን፤ ታላቁንና ከምንጊዜም እጅግ ምርጥ ውድድሮች አንዱን በማዘጋጀታቸው አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው።
ወደ ኒው ዮርክ JFK ኤርፖርት የወሰደኝ በረራ፤ በነጋታዉ ወደ ዳላስ ፎርት ዎርዝ በሰላም መልሶኛል። በዚህኛው ጉዞ በረራዬ ምንም አይነት መስተጓጎል አልገጠመዉም።
አበቃሁ!
ሐምሌ 26/2018 ዓም