የትዕግስት እንባ፣ የኃይሌ እጅ እና የኢትዮጵያዊነት ልብ - በበርሊን ጎዳና
የበርሊን ጎዳናዎች እሁድ ረፋድ መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ.ም ዓለም ላይ ባሉ ፈጣን ሯጮች እግሮች ተሞልተው ነበር። በዚያ ቀን ግን ከማራቶን ውጤት በላይ የሚታወስ አንድ ቅፅበት ተመዘገበ።
ትዕግስት አሰፋ የዓለም ክብረ-ወሰንን ለመስበር በጀመረችው የ42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ጉዞ፣ እስከ 40ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ቀጠለች። በርሊንም አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ልትመለከት የተዘጋጀች መሰለች።
ከመድረሻው ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩ ግን ያልተጠበቀ ፈተና መጣ። ቀኝ እግሯ ላይ ከባድ ጉዳት አጋጠማት። ፍጥነቷ ቀነሰ፣ እርምጃዋ ተለወጠ፣ የክብረ-ወሰን ህልሟም በመጨረሻዎቹ ሁለት ሺህ ሜትሮች መካከል የተቋረጠ መሰለ።
ታሪክ ሊሰራበት የተዘጋጀው የበርሊን ጎዳናም በዚያ ቅፅበት ሌላ ፊት አሳየ። የድል መንገድ የሚመስለው ጎዳና ወደ ጽናት ፈተና ተቀየረ።
ትዕግስት ግን አልተሰበረችም። ህመሙ በሰውነቷ ላይ ቢከብድም፣ ፍላጎቷ ሁሉ ከህመሙ በላይ ነበር። እያንዳንዱ እርምጃ እየከበዳት ቢመጣም የመድረሻውን መስመር ለማየት ቀጠለች።
2፡11፡04 በሆነ ጊዜ የበርሊን ማራቶንን ለሦስተኛ ጊዜ አሸነፈች። ይህም በሴቶች ማራቶን ታሪክ 3ኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዘገበ።
ነገር ግን የድሉ ደስታ ከህመሟ ሊለይ አልቻለም። ትዕግስት የመድረሻውን መስመር ካለፈች በኋላ በእንባ ታጅባ ተዳከመች። ለመቆምም አቅም አጣች። በዚያ የድልና የህመም ድንበር ላይ ግን አንድ እጅ ደረሰላት። ያ እጅ የኃይሌ ገብረሥላሴ ነበር።
ኃይሌ ወደ እርሷ ቀርቦ እጇን ያዘ፣ ደገፋት፣ በመጨረሻም አቀፋት። በዓለም ፊት የታየው ይህ አጭር ቅፅበት ከማራቶን ውጤት በላይ የሆነ መልዕክት ይዞ ነበር።
ኃይሌ በእነዚሁ የበርሊን ጎዳናዎች የኢትዮጵያን ስም በድልና በክብረ-ወሰን ከፍ አድርጎ ነበር። ዛሬ ደግሞ በሩጫ ሳይሆን በሰውነት ታላቅ አሻራ አስቀመጠ።
በውድድር ሜዳ ሁሉም ለድል ይሮጣል፤ ከመድረሻው በኋላ ግን የሚታየው የሰውነት ኃያልነት ነው። ኃይሌ በዚያ ቅፅበት የአትሌትነት ድልን ወደ ሰውነት አብሮነት ቀየረው።
በአንድ ወቅት በዚሁ ጎዳና ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገው ኃይሌ፣ ዛሬ ደግሞ በህመም የተዳከመችውን፣ የእርሱን አሻራ እና ታላቅነት ያስቀጠለችውን አትሌት ደግፎ ታየ።
ይህ ታሪክ ከፈጣን ሰዓትና ከሜዳሊያ በላይ የሚያሳየው አንድ እውነት አለ፤ ታላቅነት ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በሌላው የድካም ጊዜ ከጎኑ መቆምም ነው።
የስፖርት ድል በሰዓትና በሜዳሊያ ይለካል። የሰውነት ድል ግን አንዳንድ ጊዜ በተዘረጋ እጅ ይገለጣል። በዚያ ቀን ኃይሌ የሰጠው ድጋፍ ይህንኑ ይህንኑ ነው ያሳየው።
ትዕግስት አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ማስመዝገብ አልቻለችም። ነገር ግን በዚያ ቀን ከውጤት በላይ የሚቆይ ምስል ተመዘገበ፤ የአንዲት ኢትዮጵያዊት እንባ እና የአንድ ኢትዮጵያዊ የድጋፍ ልብ።
በዚያ ቀን በበርሊን ምድር የታየው የኢትዮጵያ ልብ ይህ ነበር፤ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲደክም ሌላው የሚደግፈው፣ አንዱ ሲወድቅ ሌላው እጁን የሚዘረጋለት፣ የድል ደስታንም ሆነ የህመም ጊዜን አብሮ የሚጋራ፤ የአንድነት መንፈስ እና ኢትዮጵያዊ አብሮነት ዳግም ለዓለም ታየ።
በጋዜጠኛ አዲስ የሺዋስ ለ ኢቢሲ