አምስት የቤት ስራዎች አዲስ ለሚመረጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አመራር
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እንዲታደስ ...
በአህጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረኮች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ዋነኛው ብሔራዊ የኩራት ምንጭ የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። በወንዶች የአበበ ቢቂላን ፈለግ እንዲሁም በሴቶች የደራርቱ ቱሉን ፈለግ የተከተሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አትሌቶች በትላልቅ የውድድር መድረኮች ላይ አስደናቂ ስኬቶችን በማስመዝገብ የሀገራቸውን ስም እና ሰንደቅ ደጋግመው ከፍ ማድረግ ችለዋል።
የአገሪቱ ትልቅ የኩራት ምንጭ የሆነውን የአትሌቲክስ ስፖርት በአግባቡ መምራት ያለመቻል ችግር በየግዜው በስፖርቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ እንቅፋት እየሆነ ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት በየግዜው በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አፍቃሪዎች ስፖርቱን ወደዘመናዊው የአስዳደር ደረጃ ሊያሻግሩ የሚችሉ የአመራር ብቃቱ ያላቸው ሰዎችን ለማየት ቢጓጉም ለረጅም ግዜ ጉጉታቸውን በሚጠበቀው ልክ ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ አመራሮችን ለማየት አልታደሉም፡፡ አልፎ አልፎ የመስራት አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ብቅ ሲሉም በስፖርቱ ዙሪያ ባለው የመጠላለፍ ፖለቲካ፣ ለግል ጥቅም እና ፍላጎታቸው ብቻ በሚጨነቁ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሴራ በፍጥነት ከአካባቢው ገለል እንዲሉ ይደረጋል፡፡ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታዩት የአስተዳደር ግድፈቶች ከምንግዜውም የከፉ ነበሩ፡፡ ምክንያቱ የአስተዳደር ዕውቀት እና አቅም ማነስም ይሁን የግል ስሜት እና ፍላጎቶችን መከተል በፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ ደካማ የውሳኔ አሰጣጦች፣ አቅዶ የመተግበር ችግር፣ በተገቢው መንገድ ኮሚዩኒኬት አለማድረግ እና ግልፅ ያለመሆን፣ እንዲሁም አትሌቶቻችን እና አጠቃላይ ስፖርቱን የሚመለከቱ ችግሮችን አግባብ ባለው መንገድ መፍታት ያለመቻል ችግሮች በተደጋጋሚ ታይተዋል። እነዚህ ከአስተዳደር ብቃት እና ቁርጠኝነት ማነስ ጋር የተያያዙ ችግሮች የፈጠሯቸው ክፍተቶችም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እድገት ከማደናቀፍ በዘለለ ከግዜ ወደግዜ በፌዴሬሽኑ፣ በአትሌቶች፣ በአሰልጣኞች እና በስፖርቱ እውነተኛ ደጋፊዎች ዘንድ መተማመን እንዲጠፋ እያደረጉ ይገኛሉ።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት እና በውድድሩ ወቅት እንዲሁም ከዛም በፊት በነበሩት ግዜያት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራር ዙሪያ አስተዳደራዊ ድክመቶች በስፋት ተስተውለዋል፡፡ ከድክመቶቹ አብዛኞቹ በቀደሙት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ግዜም የነበሩ እና ባሉበት ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው አመራር የስልጣን ዘመን አንዳንዶቹ ችግሮች እጅግ መስመራቸውን ሲስቱ እንደታዩም ማስተባበል አይቻልም፡፡ ለረጅም ዓመታት ባለበት የቆመው የሀገር ውስጥ ውድድሮች የጥራት ደረጃ፣ ከግዜ ወደግዜ እየተባባሰ የመጣው የልምምድ እና የውድድር ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት፣ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በተቃረቡ ቁጥር ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚታየው ውዝግብ፣ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለሚያስተዳድር ድርጅት የጀርባ አጥንት ከሚባሉ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው የመረጃ ቋት አደረጃጀት ላይ በአግባቡ አለመስራት፣ የሚወጡ የመተዳደሪያ ሕግ እና ደንቦችን ለስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ በይፋ አለማስተዋወቅ እና በአግባቡ አለመተግበር፣ እንዲሁም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ለይቶ የአጭር እና የረጅም ግዜ ዕቅድ አውጥቶ ለመተግበር አለመስራት በዋናነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ችግሮች መካከል ናቸው፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት ችግሮች እንደተከበበ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሳምንቱ መጨረሻ ታህሳስ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚያካሂደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፕሬዝደንት እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫም ያደርጋል፡፡ በሚካሄደው ምርጫ የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት አመራሮች በቀረቡት አዲስ ተመራጭ ዕጩዎች (ለፕሬዘደንትነትም ሆነ ለስራ አስፈፃሚነት ለመመረጥ ከቀረቡት ዕጩዎች አብዛኞቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚህ ቀደም በአትሌክስ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው እንደመሆኑ አዲስ ለማለት ይከብዳል) የሚተኩ ይሆናል። ከምርጫው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዕጩዎች እንደተለመደው በግዴለሽነት ተመርጠው የቀረቡ ሲሆን ከምርጫው በፊትም ሰዎችን ለመግፋት የተለመዱ የመጋረጃ ጀርባ ሴራዎች እንደነበሩ የሚያመላክቱ ነገሮች ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከምንግዜውም በከፋ የአስተዳደር ችግር ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት በሚካሄደው ምርጫ መራጮች ትልቅ ኃላፊነት ተሰምቷቸው ቢያንስ እየገዘፉ የመጡትን ችግሮች ሊቀንሱ የሚችሉ ሰዎችን እንዲመርጡ እመኛለሁ፡፡ እመኛለሁ ያልኩት ከዚህ በፊት ያየኋቸው ተሞክሮዎች በሙሉ ተስፋ እንዳደርግ የሚያነሳሱ ስላልሆኑ ነው፡፡ ጨለምተኛ ላለመሆን የቱንም ያህል ብጥርም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስልጣን የበላይ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባዔን አወቃቀር እና ለምን አይነት ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ መዘንጋት አልችልም፡፡
ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት ሰባት ግለሰቦች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ላይ ቀርበው ራሳቸውን እና አላማዎቻቸውን ያስተዋወቁበትን ፕሮግራም ተመልክቻለሁ፡፡ ከቅዳሜው የዕጩ ፕሬዝደንቶቹ እራስን የማስተዋወቅ የቲቪ ፕሮግራም ሁለት ቀን በኋላ በይፋ ባልተገለፀ ምክንያት አንደኛው እጩ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ከፕሬዝደንት ዕጩነቱ ተሰርዞ ወደ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዕጩነት እንዲገባ መደረጉ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ዕጩ ፕሬዝደንቶቹ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ አንዳንዶቹ የፌዴሬሽኑን ችግሮች ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው በሚያሳይ መልኩ ገልፀዋቸዋል፡፡ ‹‹ችግሩን ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ አካል ነው›› እንደሚባለው ዕጩ ፕሬዝዳንቶቹ ችግሮቹን ማወቃቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ከተመረጡ በኋላ ችግሩ ምንድነው ብለው ለማጣራት የሚያጠፉት ግዜ ሳይኖር በቀጥታ የሚያውቋቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ወደሚያስችለው የመፍትሔ ሀሳብ እና ትግበራ እንዲገቡ ያግዛቸዋል፡፡ ታዲያ ከዚህ ቀደምም በፌዴሬሽኑ ውስጥ የኃላፊነት ድርሻ የነበራችሁ ከተመረጣችሁ የምታስተካክሉት በእናንተ የቀደመ የአስተዳደርነት ግዜም የነበሩ ድክመቶችን ጭምር መሆኑን እንዳትዘነጉት አደራ እላለሁ፡፡
የፌዴሬሽኑ መሪዎች ተጠባቂ ፈተናዎች
ኮስተር ያለ አመራር ሊሰጥ የሚችል አቅም ያለው ፕሬዝደንት እና ፕሬዝደንቱን በትክክል የሚያግዙ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን የመምረጥ የቤት ስራውን መስራትን ለጠቅላላ ጉባኤው ትቼ፤ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እንቅስቃሴ ለብዙ አመታት በቅርበት እንደተከታተለ አንድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ደጋፊ እና የአትሌቲክስ ዘጋቢ በእኔ እይታ የመጪዎቹ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ትልቅ የቤት ስራ ሊሆኑ ገባቸዋል ብዬ የማስባቸውን ጉዳዮች ጠቅለል አድርጌ እንደሚከተለው ላመላክት፡-
1. ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እና ትግበራ
መጪው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራር ውጤታማ ስራን ለማከናወን የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ማዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ እነዚህን ዕቅዶች ለማዘጋጀትም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመፈተሽ ቁልፍ ጥንካሬዎችን፣ ድክመቶችን፣ እድሎችን እና ስጋቶችን መለየት አለበት። የአጭር ጊዜ እቅዱ ፈጣን ማሻሻያዎችና የቅድሚያ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው በጊዜያዊ የልምምድ እና ውድድር ማዘውተሪያ ችግሮች መፍቻ፣ መቀየር ያለባቸው የአሰራር ሂደቶች፣ የአሰልጣኝነት ስልጠና መርሃ ግብሮችን ማሳደግ፣ ስፖንሰርሺፕን ማጠናከር፣ በቅርቡ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች እና ሌሎችም መካተት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይችላል፡፡
የረዥም ጊዜ ስትራቴጂው ደግሞ የውድድሮች ጥራትን እና የውድድር ማዘውተሪያዎችን ማስፋፋት እና ማዘመን፣ የስልጠና ተቋማትን ማሳደግ፣ በሁሉም ዘርፎች ለአትሌቶች እድገት ቅድሚያ መስጠት፣ ዘላቂ አለም አቀፍ አጋርነትን መፍጠር እና ሌሎችም መካተት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይችላል። በሁለቱም ዕቅዶች ውስጥ የሚካተቱት ነገሮች ግልጽ፣ ሊለኩ የሚችሉ ግቦች ያሏቸው እና በጊዜ ሰሌዳዎች የተደገፉ መሆን አለባቸው፡፡ መደበኛ የአፈፃፀም ግምገማ ማድረጊያ ግዜ ሊኖሯቸውም ይገባል። አፈፃፀሞቹን የሚቆጣጠር ኮሚቴ በማቋቋም የአፈጻጸም መለኪያ ዳታዎችን እና ትንታኔዎችን በመጠቀም የሩብ አመት ግምገማን ማድረግ፤ ትግበራውን ለማሳካትም እንደ አስፈላጊነቱ ስልቶችን መቀየር ይቻላል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ መንገዶች አዘውትሮ በመገናኘት እና ግልጽ የሆነ ሪፖርትን በማቅረብም ተጠያቂነትን እና እያደገ ካለው የአለም የአትሌቲክስ ገጽታ ጋር መጣጣምን የበለጠ ለማረጋገጥ መትጋት ያስፈልጋል።
2. የፅሕፈት ቤት አሰራርን መፈተሽ እና ማዘመን
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የአለም አትሌቲክስ ስታንዳርዶችን ተከትሎ እንዲራመድ የጽህፈት ቤቱን አጠቃላይ አሰራር መገምገም እና ማዘመን ግድ ይላል። ይህም ማሻሻያ ማድረግ የሚቻልባቸውን የአስተዳደር፣ የቴክኒክ ወይም የውድድር ዝግጅት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን መለስ ብሎ መመልከትን ይጠይቃል። ከቢሮው አስተዳደራዊ እና ድርጅታዊ መዋቅር ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ በቢሮው ውሳኔ ማግኘት ለሚገባቸው ጉዳዮች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውጤታማነት እንዲሁም በአለምአቀፉ አትሌቲክስ ላይ ለሚደረጉ ለውጦች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቂ አቅም ያለ መሆኑም መታየት አለበት፡፡ በተለይ ለአትሌቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ቅልጥፍና፣ የውድድር ውጤቶችን በአግባቡ መሰነድ እና ለሚፈልጉት ሁሉ በቀላሉ የሚገኙ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አጠቃላይ የዓለም አትሌቲክስም ሆነ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መተዳደሪያ ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪዎች እንዲሁም የውድድር ሕጎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊያውቋቸው የሚገቡ ለውጦች ሲኖሩ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ማሳወቅ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ቢቻል እንዳደጉት ሀገራት የፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት የስራ ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር ተሰጥቶ በዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ዋና ዳይሬክተር እንዲመራ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት ሰራተኞችን የአፈፃፀም አቅም ለማጎልበት እና በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ዙሪያ ከሚደረጉ ለውጦች ጋር እኩል እንዲራመዱ ለማስቻልም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በቋሚነት ቢሰጡ መልካም ነው፡፡
3. የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማካሄድ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርትን ወደኋላ እየጎተቱት ይገኛሉ ብዬ ከማስባቸው ነገሮች መካከል በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራበት የሚያስፈልግ ነገር የሀገር ውስጥ ውድድሮችን በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ማካሄድ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ አለመካሄድ የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በሙሉ በተለይም የአጭር ርቀት እና የሜዳ ላይ ተግባራት ተወዳዳሪዎች ልፋት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ እያደረገ የሚገኝ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በወርልድ ራንኪንግ ነጥብ ለማስመዝገብ የሚረዱ ዋና ዋናዎቹን የሀገር ውስጥ ውድድሮች ውጤት በኤሌክትሮኒክስ የሰዓት መቆጣጠሪያ የሚደገፍ ለማድረግ መስራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የውድድሮችን ውጤቶች በዘመናዊ እና ዓለም አቀፉን መለኪያ በሚያሟላ መልኩ አለመያዝ በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለተሳትፎ የሚያበቁ ውጤቶችን (የዓለም ደረጃዎች ነጥብ) በማስመዝገቡ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ እ.አ.አ. በዲሴምበር 2022 ዓ.ም. ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በላከው መልእክት የትኛውም አይነት ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገቡ እስካልተደረጉ እና ውጤታቸው በአወዳዳሪው አካል እስካተላከለት ድረስ ውጤቶቹ በድረ ገፁ ላይ እንደማይሰፍሩ እና ለማንኛውም የስታትስቲክስ ዓላማው (የመግቢያ ደረጃዎች፣ የዓለም ደረጃዎች፣ ከፍተኛ ዝርዝሮች፣ ሪከርዶች፣ ወዘተ) እንደማይጠቀማቸው አሳውቋል። መልዕክቱ ከተላከ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ለወርልድ አትሌቲክስ የተላከ ብቸኛ የውድድር ውጤት እ.አ.አ. ከጁላይ 02 እስከ 06 /2024 የተካሄደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ውስጥ የሚያደርጋቸውን ውድድሮች በወርልድ አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገብ በማድረግ እና ውጤቶችን በሰዓቱ በመላክ የአትሌቶቹ ልፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዲያገኝ የመስራት ኃላፊነትም እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡
የኢትዮጵያን አትሌክስ ውድድሮች ለብዙ ዓመታት ስከታተል የፌዴሬሽኑ የሀገር ውስጥ የመም፣ የአገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ ውድድሮች ዓለም አቀፉን ደረጃ በጠበቀ ጥራት ሲካሄዱ ለማየት አልታደልኩም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፉን ደረጃ በጠበቀ ጥራት የተካሄዱ የስታድየም ውድድሮችን ለማየት የቻልኩት ሁለት ግዜ ብቻ ነው፡፡ እነሱም እ.አ.አ. በ2008 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታድየም የተስተናገዱት የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የአፍሪካ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ናቸው፡፡ በ2008 ዓ.ም. (በኢትዮጵያ ሚሌኒየም) ለመጀመሪያ ግዜ የታደምኩበት ትልቁ አህጉራዊ ውድድር አትሌቲክስ ላይ ብቻ አተኩሮ ወደመዘገቡ የመጣሁበትን የመጀመሪያ ስልጠና ከዓለም አትሌቲክስ ያገኘሁበትም ነበር፡፡ በዛ ውድድር ላይ የነበረው የውድድር አፈፃፀም እና የጥራት ደረጃ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይም በተመሳሳይ ጥራት እና ደረጃ ሲከናወን የማየት ጉጉት ቢፈጥርብኝም ምኞቴ እውን ሳይሆን ይኸው አስራ ሰባት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተውታል፡፡ በአጫጭር ርቀቶች እና በሜዳ ላይ የሀገር ውስጥ ውድድሮች የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደረጃውን የጠበቀ የውድድር ተሞክሮ የሚያገኙበት ዕድል ሳይፈጠርላቸው ይሄን ያህል ግዜ ማለፉ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ኬንያውያን ከእኛ በኋላ እ.አ.አ. በ2010 ዓ.ም. የተካሄደውን 17ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲያስተናግዱ እኛ በነበርንበት ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ አሁን ግን በዚህ ረገድ እጅግ የተሻለ ስራ መስራት መቻላቸውን በተግባር እያሳዩን ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ውድድሮች ማካሄድ እንዴት እንደሚቻል ለማወቅ ሩቅ ሳትሄዱ የጎረቤት ኬንያ አቻዎቻችሁን ልምዳቸውን እንዲያካፍሏችሁ መጠየቅ ነው፡፡
4. የመረጃ ቋት ማደራጀት
የመረጃ ቋት የአትሌቲክስ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በአግባቡ የተደራጀ እና ወጥነት ያለው የመረጃ ቋት ያለመኖር ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንዱ ድክመት ነው፡፡ የአትሌቶችን ምዝገባ፣ ፕሮፋይሎችን እና የሀገር ውስጥ የውድድር ውጤቶችን የሚያጠቃልል የተማከለ ዲጂታል የመረጃ ቋት ማዘጋጀት ለአንድ ሀገር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው። ለአሰልጣኞች እና የፌዴሬሽን ባለሥልጣናት የአትሌቶችን አፈፃፀም፣ እድገት እና ተሳትፎን በመከታተል በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲወስኑ ጠቃሚ መረጃዎችን ይሰጣል። በደንብ የተደራጀ የመረጃ ቋት ግልፅነትን ያሳድጋል፣ የውድድር ውጤቶችን ወጥ በሆነ መልኩ ያሳያል፣ ሪኮዶችን በአግባቡ ለመለየት፣ የአትሌቶችን ጥንካሬ እና ድክመት እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለመገምገም፣ የእድሜ ማጭበርበርን ለመቆጣጠር፣ እና የረጅም ጊዜ የአትሌቶችን እድገት ሂደት ለማወቅም ይረዳል። ከሁሉም በላይ በስፖርቱ ውስጥ የላቀ ተጠያቂነትን፣ ፍትሃዊነትን እና የአሰራር ቅልጥፍናን ያጎለብታል፡፡ ይህን ክፍተት ለማስተካከል ፌዴሬሽኑ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን የድረገፅ ማልማት እና ማዘመን እንዲሁም የአትሌቲክስ መረጃዎቹን በአግባቡ ማዘጋጀት በሚችሉ ባለሙያዎች ጥምረት ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
5. የአትሌቶች ምርጫ
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያሰለቸ ነገር ቢኖር ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የአትሌቶች ምርጫ በሚደረግ ግዜ የሚታየው ውዝግብ ነው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ፌደሬሽኑ ግልጽ የሆነ የመምረጫ መስፈርት በማስቀመጥ አስቀድሞ ለባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ በይፋ የማሳወቅ ስራውን ችላ ስለሚለው ነው፡፡ አንዳንዴ መስፈርት ቢወጣም መስፈርቱ በይፋ ሳይገለፅ ከጀርባ የግል ፍላጎቶች እየተጫኑት ችግሩን ሲያባብሰው ይታያል፡፡ ይህን ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ መቅረፍ የሚቻለው ሁሉንም የስፖርቱን ባለድርሻ ባሳተፈ ምክክር ወጥ እና ግልፅ የመምረጫ መስፈርት ሲወጣ ነው፡፡ ሁሉንም ገዢ የሆነ የምርጫ መስፈርቶች ከወጡ በኋላም በፌዴሬሽኑ ድረ-ገጽ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ገፆች እና በተለያዩ ሚዲያዎች አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመመረጥ ዝግጅት ከመጀመራቸው በፊት በደንብ መተዋወቅ አለባቸው። ሁሉም አትሌቶች እና አሰልጣኞች ሙሉ በሙሉ እንዲረዷቸው ለማድረግም መስፈርቶቹ በብዙ ቋንቋዎች ተደራሽ መሆናቸውን ማረጋገጥም በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የምርጫ ሂደቱ ለይግባኝ ሂደቶች ክፍት መሆን አለበት። መስፈርቶቹን ቀድሞ ማሳወቅ አትሌቶች የሚጠበቅባቸውን እንዲያውቁ ስለሚያደርግ ያለመግባባቶችን እምቅ አቅም ይቀንሳል፡፡ በአትሌቲክስ ማህበረሰቡ ውስጥም መተማመንን ያሳድጋል። ከፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር በፊት የታየው የፌዴሬሽኑ አመራሮች የውሳኔ ሰጪ ኃላፊነታቸውን እና ስልጣናቸውን የግል ጥቅም ግጭት ሊጫናቸው ለሚችል አካላት አሳልፈው ሰጥተው ተለማማጭ የሆኑበት አካሄድ ፈፅሞ ሊደገም አይገባም፡፡
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በትክክል የሚመራው ሰው ቢያገኝ በአለም አቀፍ አትሌቲክስ ግንባር ቀደም ደረጃውን የመጠበቅ እና የማጎልበት አቅም አለው። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን እስከዛሬም እየታዩ ላሉት አስተዳደራዊ ድክመቶች ዋነኛው አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጉዳይ የፌዴሬሽኑን ስልጣን በበላይ አካልነት የሚመራው ጠቅላላ ጉባዔ አወቃቀር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ አወቃቀር የሚቀየርበት ዕድል እስከሌለ ድረስ ስፖርቱን የሚወዱና የሚቆረቆሩለት፣ የአስተዳደር ብቃቱም ዕውቀቱም ያላቸው ሰዎች የሚመጡበት መንገድ በአመዛኙ የተዘጋ እንደሆነ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ በስፖርቱ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በሚቻለው መንገድ ለመቅረፍ ከመሞከር ባሻገር የጠቅላላ ጉባኤው አደረጃጀት ላይ፣ አዎንታዊ እና አሉታዊ ሚናዎቹም ላይ ውይይት የሚደረግበት መድረክ ቢፈጠር መልካም ነው፡፡ በየማነ ፀጋይ የሚመራው የአትሌቶች ማሕበርም አዲሶቹ አመራሮች ለአትሌቶች የበለጠ ድጋፍ የሚደረግበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ እንዲሁም ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሰሩ የበኩሉን ግፊት እና አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡