post-thumb

"ሎስ አንጀለስ ነገ ነው!" ፦ የስፖርት አስተዳደራችንን የማነጽ እና የጥፋት አዝማሚያዎችን የመታገል ግዴታ

ይህ ፅሁፍ የትኛውንም ተቋም የማይወክል፤ ጥናትም፣ ሪፖርትም፣ የምርመራ ውጤት ሳይሆን እንደ አንድ ባለሙያ በኃላፊነት ስሜት ለውይይት በር ለመክፈት ብቻ የተፃፈ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ፤

 

  1.   እንደ መንደርደሪያ

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ “ማንነት” የሚሰጠው ትርጉም እጅግ ላቅ ያለ ሲሆን፤ ዜጎች የብሄር ማንነት፣ የቋንቋ ማንነት፣ የሐይማኖት ማንነት፣ የፆታ ማንነት እና ሌሎችም የማንነት አውዶችን ተጠቅመው ራሳቸውን በማደራጀት ለቆሙለት አላማ ፀንተው ይታገላሉ፤ የትግሉም ፍሬ በአግባቡ ለሐገር እና ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ያደርጋሉ፡፡ 

ከላይ ከተዘረዘሩ ማንነቶች በተጨማሪ “ሙያ” አንዱ የማንነት ዘውግ ሲሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ የሙያ ማንነት ውስጥ እራሳቸውን በመለየት ሙያቸውን ለማስፋፋት በዚህም የሐገር፣ የህዝብ እና ግለሰባዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ 

ይህ የሙያ ማንነት ጥያቄ ለስፖርትም የሚሰራ ሲሆን ሙያው ሐገርን እንዲጠቅም ህዝብን እንዲያገለግል ትውልድን እንዲያንፅ ሆኖ ከተደራጀ እና ከተመራ የሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በአንድ ሐገር ልማት፣ አብሮነት፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ህብረተሰባዊ ስነልቦና ግንባታ፣ አለም አቀፍ ግኑኝነት፣ ሰላም፣ ምስል ግንባታ፣ ጤና፣ በጎ ትርክት መፍጠር ላይ እና ወዘተ ስፖርት የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡

በተቃራኒው በአግባቡ ያልተመራ ስፖርት በአንድ ሐገር ጥቅም እና የህዝብ ፍላጎት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከሜዳሊያ እና ከዋንጫ ማጣት በዘለለ፣ ከተሳትፎ እና ከውጤት ክርክሮች በተረፈ ከባድ ሀገራዊ ችግር እንደሚያከትል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሙያውም እየከሰመ እና እየቀነጨረ የመሄድ እድሉ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ 

 

  1. የብራንድ ቀውስ

ከቶኪዮ እስከ ፓሪስ በታዩት ሁለት ኦሎምፒያዶች ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሎም የኢትዮጵያ ስፖርት ከሜዳሊያ እና ከውጤት በዘለለ የብራንድ ክራይስስ ወይም የብራንድ ቀውስ አጋጥሞታል ብዬ አስባለሁ፡፡ 

ለወትሮው በአበበ ቢቂላ ባዶ እግሮች የሚታወሰው ኦሊምፒክ፣ አረንጓዴው ጎርፍ ምልክቱ የነበረው ኦሊምፒክ፣ በለቅሶ የሚታጀበው ብሄራዊ መዝሙር፣ በዜጎች ደማቅ አቀባበል የሚወሳው ኦሊምፒክ እና ሌሎችም መልካም ዝናዎች ተሸርሽረው አሁን በአተካሮ፣ በነውር፣ በቅሌት፣ አለፍ ሲልም በወንጀል አዝማሚያዎች ታጅቦ የዜጎችን እምነት በሚሸረሽሩ ባህሪያት ተጥለቅልቋል፡፡ ይህ የብራንድ ቀውስ የስፖርቱን ህልውና የሚፈታተን መሆኑን ተከትሎ ከተጋረጠበት አደጋዎች መሀከል እንደማሳያ

  • ማህበረሰቡ ለስፖርቱ ያለውን ቀናዊ አመለካከት እንዲያጣ፤

  • ባለሀብቱ በስፖርት ዘርፍ መሳተፍ እንዲያቆም፤

  • ድርጅቶች ስፖርቱን ስፖንሰር ከማድረግ እንዲቆጠቡ፤

  • አመራር እና መንግስት በስፖርቱ እንዲሰላች እና ድጋፉን እንዲቀንስ፤ 

  • ጤናማ አማተር አገልጋዮች ስፖርቱን እንዲርቁ በተቃራኒው ጤናማ ያልሆኑት እንዲበዙ፤

  • ባለሙያው በቤቱ እንዲቀመጥ እና እንዲሸሽ፤

 

  1. የኢትዮጵያ ስፖርት አስተዳደር

ምንም እንኳን ሐገራት እንደሚመሩበት የፖለቲካ ርዕዮተ አለም የተለያየ የስፖርት ፍልስፍና እና የተለያየ አስተዳደር ቢከተሉም ሁሉም በሚባል መልኩ ከስፖርት ተጠቃሚ ለመሆን አቅደው እና አልመው ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡

ሐገራችን ኢትዮጵያም የስፖርት አጠቃላይ ፍልስፍናዋን በፖሊሲ ቃኝታ፣ በተለያዩ የአሰራር ስርአቶች እና የህግ ማዕቀፎች አስቀምጣ፣ አደረጃጀት፣ አመራር እና ባለሙያ መድባ መንቀሳቀስ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ በዚህም ትይዩ የስፖርት አስተዳደር ስርአት በመዘርጋት መንግስታዊ እና ህዝባዊ አደረጃጀቶች ተደጋግፈው ስፖርቱን እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል፡፡ 

ሆኖም ግን በሁለቱም ወገን ተዘውትረው በሚታዩ የአስተዳደር ክፍተቶች ምክንያት ሙያው ማደግ ያለበትን ያህል እንዳያድግ፤ ሐገር እና ህዝብም ከሙያው መጠቀም የሚገባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ወረት እንዳይኖር ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ገራገር ልዩ የስፖርት ባህሪያት ናቸው፡፡ 

 

  1. ገራገር የስፖርት ልዩ ባህሪያት

ስፖርት ሁለት ገራገር ልዩ ባህሪያቶች አሉት፡፡ 

አንደኛው ህዝባዊነቱ ወይም ህዝባዊ መሰረት መሆኑን ተከትሎ ስፖርት ከተለያየ የሙያ መስክ የሚመጡ፣ የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ አረዳድ፣ ክህሎት፣ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በአንድ ላይ እንዲመሩት እንዲያስተዳድሩት የሚፈቅድ ነው፡፡ ይህ የመሪዎች ብዝሀነት ስፖርቱን በእጅጉ ይጠቅመዋል ተብሎ ቢታሰብም አሁን አሁን ግን ፍፁም የማይዋሀዱ ውሀ እና ዘይት የሆኑ ማንነቶች፣ ፍፁም ተቃርኖ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በአንድ ላይ ሲመጡ እና ለመቀያየጥ ሲዳዳቸው ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ፍልስፋናው በከፈተው በር፤ ገራገርነቱ በወለደው ምንነቱ ምክንያት ተጎጂ እየሆነ መጥቷል፡፡

ሁለተኛው የስፖርት ገራገር ልዩ ባህሪ አለም አቀፋዊነቱ መሆኑን ተከትሎ ከመንግስት እይታ ሲጠፋ እና ከለላ ሲነፈገው ይስተዋላል፡፡ በስፖርት መንግስት ጣልቃ አይገባም፣ እኛ የምንከተለው አለም አቀፍ መስመርን ነው፣ ይህ ህዝባዊ አደረጃጀት ነው፣ ተጠሪነታችን ለኢትዮጵያ መንግስት ሳይሆን ለመረጠን ጉባኤ እና ስዊዘርላንድ ለሚገኝ አካል ነው እና ሌሎች የመሳሰሉ የስፖርቱን ገራገር ባህሪያት እንደምሽግ በመጠቀም ህዝባዊ ተቋማትን ላልተፈለገ አላማ የማዋል በዚህም የሀገርን፣ የህዝብን እና የትውልድን ጥቅም የመንፈግ አዝማሚያዎች እየበረከቱ መጥተዋል፡፡

 

  1. የፀና መንግስታዊ አደረጃጀት የመፍጠር ውስንነት

ምንም እንኳን ስፖርት ህዝባዊ ቢሆንም የኢትዮጵያ ስፖርት የመንግስት ተገንነትን ለመላቀቅ እጅግ በጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ጠንካራ እና ተሰሚነት ያለው የስፖርት ተቋማትን መፍጠር ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርት ላለፉት ረዥም አመታት በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተፐወዘ እና እየተቀየጠ ወጥነት ያለው ማንነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ ስፖርት ኮሚሽን፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ባህል እና ቱሪዝመ ስር ያለ ተጠሪ ኮሚሽን እና የመሳሰሉትን አደረጃጀቶች እየተሰጡት በአንድ ሊፀና አለመቻሉ ተፅእኖው እንዲገታ፣ ተሰሚነቱ እንዲቀንስ እና ወጥነት ያለው ከለር እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ 

ከተቋሙ በተጨማሪ የመንግስት አመራሮች በቦታው ላይ በፍጥነት መቀያየር እራሱን የቻለ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ከፍተኛ አመራሮችን የመለወጥ ስራ የራሱ የሆነ ተገቢ ፖለቲካል ግብ እንዳለው ብረዳም በስፖርት ዘርፉ የሚታየው የአመራሮች ልውውጥ ፍጥነት ግን ተቋምን ለማነፅ በሚያስችል መልኩ ሆኖ አይሰማኝም፡፡ እኔ በግል እንኳን ባለፉት 5 አመታት ከ9 አመራሮች ጋር አብሮ የመስራት እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ 

በዚህም ምክንያት ማህበራት እና በስፖርቱ ውስጥ ስር የሰደዱ አማተሮች ከመንግስት በላይ የመሆን አዝማሚያዎችን ሲያሳዩ ተስተውሏል፡፡

 

  1. የስፖርት የወንጀል አዝማሚያ መታየታቸው 

በአንድ ሐገር እድገት፣ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ወንጀልን መከላከል፣ ሙስናን መዋጋት እና ሌሎች ጥፋቶችን መቆጠጣር እንዲሁም የወንጀል ፍትህ ስርአትን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሲሆን ዜጎች በተሰማሩበት መስክ የላባቸውን እንዲያገኙ፣ የሙያ መስኮች እንዲጎለብቱ ብሎም ሐገር ከዘርፎች ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ 

ሐገራት ከሚጋፈጡት ከእነዚህ ወንጀሎች መሀከል የስፖርት ሙስና እና ተያያዥ የስነ ምግባር ጉድለቶች በተለያዩ ሐገራት፣ በተለያየ መልኩ ለመንሰራፋታቸው በተለያዩ ጥናቶች ላይ ቀርቧል፡፡ የጥፋቱ ደረጃ፣ መንስኤ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሐገር ሐገር፣ ከስፖርት ስፖርት፣ ከተቋም ተቋም ይለያይ እንጂ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ስፖርት ለብልሹ አስተዳደር ተጋላጭ ከሆኑ ዘርፎች ውስጥ በጉልህ ይጠቀሳል፡፡

እንደ ሌሎች ሐገራት ሁሉ የኢትዮጵያ ስፖርትም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ እና ለሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና ተያያዥ የስነምግባር ጉድለቶች ተጋላጭ እንደሆነ በተለያየ መልኩ ተገልፆል፡፡ ምንም እንኳን በህግ፣ በአሰራር፣ በአደረጃጀት እና በተለያዩ ስልቶች ይሄንን የሙስና አስከፊ ገፅታ ለመዋጋት ጥረት ቢደረግም ከድርጊቱ ውስብስብነት እና ተለዋዋጭነት እንዲሁም አለም አቀፋዊ ይዘት አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ለመግታት አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ ስፖርቱን እና በስፖርቱ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎችን የሚጎዳ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሐገር ሐብት ብክነት ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር፣ ከፍ ሲልም በሐገር ገፅታ እና ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ላይ አሉታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት በጉልህ ያሳያል፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ላዘጋጀው የፓናል ዲስከሽን እንደ መነሻ የቀረበ የግል አስተያየት

 



Samuel Sleshi

Sports science expert

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.